ተቋርጦ የቆየው የመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት የውጭ ሃገር የስራ ስምሪት ነገ ይጀመራል

ለአምስት አመታት ያህል ተቋርጦ የቆየውና ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሃገራት የሚደረገው የውጭ ሃገር የስራ ስምሪት ነገ በይፋ እንደሚከፈት የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ወደ ውጭ ሃገር ሄደው መስራት ለሚፈልጉ ዜጎች ከዚህ በፊት በስራ ስምሪት አዋጅ ቁጥር 104/90 እና አዋጅ ቁጥር 632/2001 አውጥቶ ሥራ ላይ አውሎ እንደነበር ይታወሳል።

ይሁን እንጅ አዋጁ በስራ ላይ በነበረበት ወቅት ወደ ውጭ ለሥራ የሚሄዱ ዜጎች ተገቢውን መብትና ክብራቸውን ከማስጠበቅ አኳያ ክፍተት እንደነበረበት፥ የሚኒስቴሩ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ይርጋለም ተናግረዋል።

አዋጁ ላይ የነበረው ክፍተት ለህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መንገድ በመክፈቱና በዜጎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲደርስ በማድረጉ ተቋርጦ እንደነበርም አስታውሰዋል።

በወቅቱም ዜጎች ተገቢውን የሙያና የክህሎት ስልጠና ሳያገኙ ይሄዱ ስለነበር በተቀባይ ሃገራት፥ ገበያ ላይ ተወዳዳሪ መሆን እንዳልቻሉም አንስተዋል።

መንግስትም ይህን ጉዳይ በመመልከት የአሠራር ክፍተቱ እስከሚስተካከልና ደንብና ሥርዓት እስከሚበጅለት ድረስ የውጭ ሃገር የስራ ስምሪትን ከጥቅምት 14 ቀን 2006 ዓ.ም ጀምሮ እንዲዘጋ አድርጓል ነው ያሉት።

ሚኒስቴሩ አዋጁ በሚደነግገው መሰረት ዜጎች ሰብዓዊ መብታቸው ተጠብቆ ለሥራ እንዲሰማሩ ለማድረግ ከተቀባይ ሃገራትና እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል።

አሁን ላይም የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በመጠናቀቃቸው ከተቀባይ ሃገራት ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት በተፈረመባቸው ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ኳታርና ዮርዳኖስ የውጭ ሃገር የስራ ስምሪት ነገ እንደሚጀመር የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።

banner ad

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *