የኢትዮጵያና የሱዳን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሞች ተወያዩ

ነሀሴ16፣2ዐ1ዐ

የኢትዮጵያና የሱዳን መከላከያ ሠራዊት የቴክኒክ ኮሚቴና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሞች ልዩ የጋራ የውይይት መድረክ በሱዳን ካርቱም ከተማ ከነሀሴ 7 እስከ 1ዐ/2ዐ1ዐ ዓ.ም ተካሄደ፡፡

 

Screen Shot 2018-08-22 at 5.04.08 PM

በሁለቱም ሀገራት የመከላከያ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሞች የተመራው ይህ የውይይት መድረክ በጋራ ሰላም እና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ አተኩሯል፡፡

በውይይቱ ከአሁን ቀደም በሁለቱ ሀገሮች ስምምነት መሰረት የተደራጀው የጋራ የድንበር ኃይልን አጠናክሮ ለማደራጀትና የጋራ ኃይሉን የቦታ አቀማመጥ ለማስተካከል ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ሠዓረ መኮንን እና የሱዳን መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ዶ/ር ከማል አብዱልማሩፍ በጋራ በሰጡት መግለጫ በየሀገራቱ ከሚገኙ የፀጥታ ተቋማት ጋር በጋራ ኮሚቴ ተደራጅቶ በመስራት የሁለቱ ሀገሮች የድንበር አካባቢ ሰላምና ደህንነትን የማረጋገጡ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ውይይቱን የተከታተሉት የመከላከያ የውጭ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ደስታ አብቼ ተናግረዋል፡፡

 

በድንበር አካባቢ የሚስተዋሉ ህገ-ወጥ የሰዎችና የጦር መሳሪያ ዝውውርን በጋራ መከላከል በሚቻልባቸው አጀንዳዎች ላይ የሁለቱም ሀገራት ኢታማዦር ሹሞች ስምምነት ላይ መድረሳቸውንም ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም ሁለቱ ሀገሮች በድንበር አካባቢ የመረጃ ልውውጥ አጠናክሮ ለመቀጠልና የረጅምና የአጭር ጊዜ ስልጠናዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ጀኔራል መኮንኑ ጠቁመዋል፡፡

የተቋቋመው የጋራ ኮሚቴ የድንበር አካባቢ ግጭቶችን መፍታት የሚያስችሉ ሥራዎችን የሚያከናውን ሲሆን በቀጣዩ ዓመት ጥቅምት ወር በሚካሄደው ውይይት ኮሚቴው ሪፖርት እንደሚያቀርብ ሜጀር ጀነራል ደስታ አብቼ ገልፀዋል፡፡

 

መረጃውን ያደረሰን የመከላከያ ኢንዶክትሪኔሽን እና ሕዝብ ግንኙነት ነው፡፡

banner ad

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *