ደኢህዴን መንግስት በተለያየ ወንጀል በተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደሚደግፍ አስታወቀ

መንግስት በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ስልጣንን ተገን በማድረግ ህገ-ወጥ ድርጊቶችን በፈፀሙ ተጠርጣሪዎች ላይ የጀመረውን እርምጃ እንደሚደግፍ ደኢህዴን አስታወቀ።

የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥቷል።

በመግለጫውም ከድርጅቱ ተልዕኮና ባህሪ እጅግ ባፈነገጠና በተቃረነ አግባብ የሚፈፀሙ የኢኮኖሚ አሻጥሮችን፣ የዜጎችና የቡድኖች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰቶችን እንዲሁም ስልጣንን ለሽብር ተግባር የማዋል ድርጊቶችን ደኢህዴን በእጅጉ ይኮንናል ብሏል።

በዚህ ድርጊት ውስጥ የተሳተፉ አካላትም ተገቢው ህጋዊ እርምጃ ይወስደባቸው ዘንድ ድርጅቱ የበኩሉን ጥረት እንደሚያደርግም ገልጿል።

ድርጅቱ በዚህ መሰል ህገ ወጥ ድርጊቶች ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች ወይም ሀይሎች የትኛውንም ብሄር፣ ብሄረሰብ፣ ህዝብ የማይወክሉ ከመሆናቸውም ባሻገር፥ ህብረተሰባዊ ለውጥን ለማፋጠን የተዘረጋውን መንግስታዊ ስልጣን ለግል ጥቅማቸው ማስከበሪያነት የተጠቀሙ በመሆኑ ድርጊቱን በጽኑ የሚቃወም መሆኑን አስታውቋል።

በሀገር እና በክልል ደረጃ በታላቅ የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ እንገኛለን ያለው ድርጅቱ፥ ለዚህ የለውጥ ሂደት ዳር መድረስም የድርጅቱ አባላት፣ ደጋፊዎች እና ህብረተሰቡ በአስተሳሰብና በድርጊት በተቀራረበ ሁኔታ በመቀናጀት የለውጡን ፍሬ ለማየት በርትተው እየሰሩ መሆኑንም ጠቁሟል።

የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ወደማይቀለበስ ደረጃ ለማድረስም የህግ የበላይነት በተግባር በማረጋገጥ የድርጅቱንና የመንግስትን ስልጣን ተገን አድርገው ህገወጥ ጥፋት በሚፈፀሙ አካላት ላይ አስተማሪ እርምጃ መውሰድ ተገቢ ነው ብሏል።

ድርጅቱ ከህዝባዊ ባህሪ በማይመነጭና ከማህበራዊ፣ ከኢኮኖሚያዊና ከፖለቲካዊ ዓላማዎችና ፕሮግራሞች ፍፁም በተፃራሪ መልኩ የተሰማሩ ግለሰቦችንና ግብረ አበሮቻቸውን በህግ ቁጥጥር ስር ለማዋል የተጀመረው ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያሳሰበ ሲሆን፥ ንቅናቄው ድርሻውን በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ለመወጣት መዘጋጀቱንም ገልጿል።

መንግስታዊና ህዝባዊ ሀላፊነታቸውን ወደ ጎን በመተውና ሥልጣንን መከታ በማድረግ በከፍተኛ ምዝበራ፣ በሰብአዊ መብት ጥሰትና በሽብር ተግባር የተጠረጠሩ ግለሰቦች፥ ህጋዊ መንገዱን በመከተል በቁጥጥር ስር ማዋሉና ተገቢውን ቅጣት የማሳረፉ ሂደትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን አቅርቧል።

የለውጡን መሰረት ማስፋትና ወደ ላቀ ደረጃ የማሸጋገሩ ሂደት አልጋ በአልጋ በሆነ ሁኔታ ሊራመድ እንደማይችል በውል የሚገነዘበው ድርጀቱ፥  ህገወጦችን የመለየቱና እርምጃ የመውሰዱ ተግባር ህብረተሰባዊ ለውጡን ለማረጋገጥ ካለው ፋይዳ አንፃር በቁርጠኝነትና በግልጸኝነት መንፈስ ሊፈጸም ይገባል ነው ያለው።

banner ad

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *