ፖሊስ አቶ ያሬድ ዘሪሁንን በከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የሙስና ወንጀል እንደጠረጠራቸው ገለፀ

መርማሪ ፖሊስ የቀድሞው የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ምክትል ሀላፊ እና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል አቶ ያሬድ ዘሪሁንን በከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የሙስና ወንጀል እንደጠረጠራቸው ገለፀ።

ተጠርጣሪው ዛሬ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ የወንጀል ችሎት ቀርበዋል።

መርማሪ ፖሊስ አቶ ያሬድ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የቀድሞ ሀላፊ ጋር በመመሳጠርና ቀጥተኛ ትዕዛዝ በመቀበል በርካታ ኢ- ሰብዓዊ ድርጊት መፈፀማቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።

በሽብር የተጠረጠሩ ግለሰቦች ስውር እስር ቤት ቤት እንዲገቡ፣ ብልታቸው በፒንሳ እንዲሳብ፣ ፣ ብልት ላይ ሀይላንድ ማንጠልጠል፣ እርቃናቸውን ጉንዳን ማስበላትና ሌሎች ኢ – ሰብዓዊ ድርጊት  እንዲፈፀም ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውንም መርማሪ ፖሊስ ገልጿል።

ግለሰቦች ወደ ኤርትራ ሄደው ህገ ወጥ መሳሪያ እንዲያስገቡ በማቀነባበር ህዝብ እንዲሸበርና ተጠርጣሪዎች ላይ እንዲሳበብ ማድረግ በሚል ወንጀል እንደጠረጠራቸውም ፖሊስ አስታውቋል።

ተጠርጣሪው አቶ ያሬድ በበኩላቸው ከህግ አማካሪያቸው ጋር መገናኘት እንደሚፈልጉ በመግለፅ ለሚቀጥለው ማክሰኞ ቀጠሮ ይሰጠኝ ሲሉ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

በተጨማሪም ከማንም ጋር እንዳልገናኝ እየተደረኩ ነው፤ አንድ ክፍል ውስጥ ብቻዬን ነው የታሰርኩት ሲሉም ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አቅርበዋል።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ ተጠርጣሪው ከማንም ጋር እንዳልገናኝ እየተደረኩ ነው፤ አንድ ክፍል ውስጥ ብቻዬን ነው የታሰርኩት ሲሉ ያቀረቡትን ያስተባበለ ሲሆን፥ ተጨማሪ 14 ቀን የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

የግራ ቀኙን የተመለከተው ፍርድ ቤቱም ተጠርጣሪው ከህግ ባለሙያ ጋር እንዲገናኙና የተጠየቀው የ14 ቀን ቀጠሮ ላይ ብይን ለመስት ለፊታችን ማክሰኞ 8 ሰዓት ቀጠሮ ሰጥቷል።

በአሁኑ ወቅት ኮሎኔል አሰፋ ዮሀንስ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በችሎቱ ቀርበዋል።

ኮሎኔል አሰፋ፥ አሰፋ የፓወር ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ሃላፊ ሆነው ሲሰሩ በበለስ 1 ስኳር ልማት ፕሮጀከት ለሃይል ተከላ ከአንድ የቻይና ኩባንያ ጋር በ49 ሚሊየን 920 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ውል እንዲታሰርና ከዚያም ተጠርጣሪው በራሳቸው ፍቃድ ክፍያው ወደ 55 ሚሊየን 640 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ከፍ እንዲል በማድረግ።

በዚህም ክፍያውን በመፈጸምና ኩባንያው ስራውን ሳይሰራ ከሃገር እንዲያመልጥ በማድረግ የህዝብ ሃብት በማባከን እና በማሸሽ ተጠርጥረዋል።

በተጨማሪም ለሌላ የውጭ ኩባንያ 6 ሚሊየን 400 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ተጨማሪ ውል በማሰር 1 ሚሊየን 920 ሺህ የአሜሪካ ዶላር እንዲከፈለው በማድረግና ኩባንያው ስራውን ሳይሰራ ገንዘቡን ይዞ ወጥቷል።

ተጠርጣሪው ገቢየ 8 ሺህ ብር ነው ሌላ ሀብት የለኝም ብለዋል፤ ፖሊስ በበኩሉ ከፍተኛ ተከፋይ መሆናቸውን በመጥቀስ ሀብታቸውን ለማጣራት ጊዜ ይሰጠኝ በማለት ጠይቋል።

ኮሎኔል አሰፋን በተመለከተ ወደፊት ሀብታቸው የሚጣራ ሆኖ እስከዛው የመንግስት ጠበቃ እንዲቆምላቸው በማዘዝ ለማክሰኞ 9 ሰዓት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

 

በባሃሩ ይድነቃቸው

banner ad

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *